ቀጥታ፡

የምርጫ ቁሳቁሶችን በማሟላት መራጮችን እየተጠባበቅን ነው 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶችን በማሟላት ለነገው ምርጫ መራጮችን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገለጹ።

በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም መራጮች ወደ የምርጫ ጣቢያዎች ለመራጭነት ሲሄዱ ማንነታቸውን የሚገልፅ ማስረጃና የመራጭነት ካርድ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝቧል።

በተመሳሳይ በምርጫዬ መተግበሪያ ወይም በድረ ገፅ የተመዘገቡ ደግሞ የምርጫ ካርዱን ቅጅ በስልክ ወይም በታተመ ቅጂ ይዞ መቅረብም እንደሚኖርባቸው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል-20 የምርጫ ጣቢያዎችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ቅኝት አድርጓል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሀሴት እንግዳ ማረፊያ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ብሩክ አማን፤ በጣቢያው ለምርጫ አስፈላጊ የድምፅ መስጫ ወረቀት፣ ኮሮጆና ሌሎች ቁሳቁሶች መሟላታቸውን አስታውቀዋል።

በክፍለ ከተማው የወረዳ-01 ደጓ እናት ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ሀና ዳምጤ በበኩላቸው፤ ሁሉም አይነት የህብረተሰብ ክፍሎች በተመቻቸ ቦታ መምረጥ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው ቁሳቁስና ግብዓቶችን በማሟላት መራጮች የሚጠለሉባቸው ማርፊያ ዳሶች ጭምር ተዘጋጅተዋል ያሉት ደግሞ የጀሞ አንድ ኮንዶሚኒየም ብሎክ 92 የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ታሪኩ ደርሶ ናቸው።

የየምርጫ ጣብያ አስተባባሪዎቹ አያይዘውም ማህበረሰቡ ነገ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመምጣት ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም