ቀጥታ፡

ለመምረጥ የድምፅ መስጫ ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመምረጥ ድምፅ መስጫ ዕለቷን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።

በእለቱም 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 የምርጫ ካርድ የወሰዱ መራጮች ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብለው ያመኑበትን አካል እንደሚመርጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም ነገ የሚካሄደውን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምርጫ ክልል-19 ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ቅኝት አድርጓል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት በነገው እለት በሚካሄደው ምርጫ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል መሰረት ረጋሳ እንዳለችው፤ የምርጫ ካርዷን አውጥታ ቀኑን በመጠባበቅ ላይ መሆኗን ተናግራለች።

ሌላው ነዋሪ ሰኢድ አሊ በበኩላቸው፤ የምርጫ ካርዳቸውን በወቅቱ ወስደው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን  ገልጸው፤ ነገ በማለዳ በመውጣት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እመቤት ፈይሳ እንደገለጸቸው፤ እንደዜጋ ለሀገር ዕድገትና ልማት ይበጃል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ነው ያለችው።

ሌላኛው ነዋሪ አስፋው አሰፋ በበኩላቸው፤ የምርጫውን ዕለት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን በመግለጽ በማለዳ በመውጣት ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም