ቀጥታ፡

የባህርዳር ምርጫ ክልል ምርጫ ጣቢያዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የባህርዳር ምርጫ ክልል ምርጫ ጣቢያዎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።

ኢትዮጵያ ነገ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ታካሂዳለች።

ኢዜአ በባሕርዳር የምርጫ ክልል የተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ተንቀሳቅሶ የዝግጅት ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ ቃኝቷል።

የምርጫ ጣቢያዎቹ አስተባባሪዎች እንደገለፁት ከትናንን ጀምሮ የምርጫ ቁሳቁስን ወደ ጣቢያ የማሰራጨት፣ ለምርጫው አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በፋሲሎ ክፍለ ከተማ 15/1ሀ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ሄለን ዓለሙ፥ የመራጮች ድምፅ መስጫ ኮሮጆና ሌሎችም ቁሳቁሶችን ተረክበው ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለመራጮች የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የድንኳን ተከላና ወንበሮች በበቂ ሁኔታ መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

በግሽ ዓባይ ክፍለ ከተማ የ02/1 ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ፍስሐ ገረመው፥ የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚዎችና የቁሳቁስ ዝግጅት ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተማ የአንድ በአንድ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አዘዘው ጠገናው፥ በጣቢያው 1 ሺህ 500 መራጮች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በነገው ዕለት ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንደ ጣቢያ የተሟላ የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።

የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎቹ አክለውም ነገ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ መራጮች ድምፅ መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

በየምርጫ ጣቢያው ታዛቢዎች በተገኙበት የምርጫ ሂደቱን ለማስፈጸም የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም