ቀጥታ፡

በአርባ ምንጭ ምርጫ ክልል ሥር ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ለምርጫው ዝግጅቶች ተጠናቀዋል

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በአርባ ምንጭ ምርጫ ክልል ሥር በሚገኙ 227 የምርጫ ጣቢያዎች በነገው እለት ለሚካሄደው ምርጫ የዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተገለጸ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ምርጫ ጣቢያ ሃላፊዎች እንደገለጹት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ጣቢያዎቹ ለነገ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ዝግጁ ተደርገዋል። 

በአርባ ምንጭ ከተማ የጫሞ ካምፓስ ምርጫ ጣቢያ ሃላፊ ሰለሞን ሳዳማ ለምርጫው ስኬታማነት አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በዝግጅት ሥራው ድንኳን ተከላና አጠቃላይ የምርጫ ቁሶች በተሟላ ሁኔታ የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛዋ በከተማው የየትነበርሽ ወፍጮ ቤት ምርጫ ጣቢያ ሃላፊ መሠረት በቀለ ከምርጫ ቦርድ የመጡ ቁሶችን መረከባቸውን ጠቅሰው ለድምጽ አሰጣጥ ሂደት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

የምርጫ ሃላፊ፣ የመዝገብ ሹምና ታዛቢዎች የሚቀመጡበት ስፍራ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

ለነገው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የሚያስፈልጉ ቁሶች ዝግጁ ናቸው ያሉት ደግሞ የአኩኩሉ ምርጫ ጣቢያ ሃላፊ አቶ እንዳልካቸው ምናሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም