ቀጥታ፡

በሻሸመኔ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ዝግጅት በተሟላ ሁኔታ ተጠናቋል

ሻሸመኔ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በሻሸመኔ ከተማ በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ነገ ለሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የምርጫ ዝግጅቱ በተሟላ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለፀ።

የሻሸመኔ አንድ ምርጫ ክልል ኃላፊ አቶ አማረ ተክልዬ እንደገለፁት በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 145 ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭትና ሌሎች ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

በነገው ዕለት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ለማስጀመር የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት በሁሉም ጣቢያዎች ላይ ተደርጓል ብለዋል።

በምርጫ ክልሉ የአዋሾ አጂፕ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ የሆኑት ወይዘሮ መዲና በሪሶ በጣቢያው የምርጫ ቁሳቁስ በትናንትናው ዕለት ገብቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለትም ድንኳኖችን የማዘጋጀትና የተከላ ሥራ ተከናውኖ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የሻላ ጀርባ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ የሆኑት አቶ መሀመድ ጩራ ለድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ሁሉም መግባታቸውን መመልከታቸውን ገልፀዋል።

ለምርጫ አስፈፃሚዎችና ታዛቢዎች የሚሆኑ ቦታዎችና ቁሳቁስ ዝግጁ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

መራጮች ለዝናብም ሆነ ለፀሐይ እንዳይጋለጡ የድንኳን ተከላ እንዲሁም ወንበር የማዘጋጀት ሥራም ተከናውኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም