በምርጫ ክልሎቹ ሥር ባሉ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ለማስፈፀም አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫ ክልሎቹ ሥር ባሉ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ለማስፈፀም አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በወላይታ ሶዶ ከተማ ሶዶ ዙሪያ ቁጥር-1 እና ሶዶ ዙሪያ ቁጥር-2 ምርጫ ክልሎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ለማስፈፀም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የምርጫ ጣቢያ ሃላፊዎች ተናገሩ።
ለነገው ጠቅላላ ምርጫ በጣቢያዎቹ የምርጫ ቁሳቁስን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶችን በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር የጣቢያዎቹን ኃላፊዎች አነጋግሯል።
የምርጫ ጣቢያ ሃላፊዎቹ እንደገለጹት የድምፅ መስጫ ቁሶችን በመረከብ የነገውን ምርጫ ለማስፈፀም የዝግጅት ሥራ አጠናቀዋል።
ከጣቢያ ኃላፊዎቹ መካከል በወላይታ ሶዶ ከተማ ሶዶ ዙሪያ አንድ ምርጫ ክልል ኪዳነምህረት ቀበሌ አሜን ሥጋ ቤት መንደር ምርጫ ጣቢያ ሃላፊ አቶ እንድሪያስ ዋትሮ እንደገለጹት፣ የድምፅ መስጫ ቁሶችን በወቅቱ በመረከብ ምርጫ ለማስፈጸም የሚያስችል ዝግጅት አድርገዋል።
በጣቢያው ምርጫ ማስፈፀም የሚያስችሉ ግብአቶች እንዲሁም የሰው ሃይል ተሟልቶ በነገው እለት ለመራጮች ቀልጣፋ መስተንግዶ ለመስጠት የተሟላ ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል።
በሶዶ ዙሪያ ሁለት ምርጫ ክልል የብሩህ ተስፋ ስቴዲየም ዕድር መንደር ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አክሊሉ ኢጃጆ እና የግሪንላድ ሆቴል ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ብሩክ ምልኪያስ በበኩላቸው ለነገው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በምርጫ ጣቢያቸው ምርጫ ማከናወን የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ከመረከብ ባለፈ አስፈላጊ ዝግጅቶች ተደርገው ለነገ መራጮችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።