ቀጥታ፡

የኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪዎች በአዲስ አበባ የቅድመ ምርጫ ምልከታዎችንና የትብብር ስራዎችን አስመልክቶ የጋራ ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ የኢጋድ እና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪዎች በአዲስ አበባ የቅድመ ምርጫ ምልከታዎችንና የትብብር ስራዎችን አስመልክቶ የጋራ ውይይት አድርገዋል።

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ፣ ከቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ከሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ መክረዋል።

የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪዎቹ ያደረጉት ውይይት ከምርጫው በፊት የተደረጉ ምልከታዎችን ለመለዋወጥና የታዛቢዎችን የስምሪት እቅድ ለመገምገም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ ግልጽ እና ሁሉንም ያካተተ የምርጫ ሂደት እንዲኖር የጋራ ቁርጠኝነታቸውንም አረጋግጠዋል።

ዶክተር ስፔሲዮዛ እና ኡሁሩ ኬንያታ በየራሳቸው የልዑካን ቡድኖች መካከል ሊኖር ስለሚገባው የቅንጅት አሰራር በሰፊው መክረዋል።

ሁለቱ የታዛቢ ቡድኖች የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ የሚያዘጋጁትን የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ሪፖርት ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በጋራ ለመግለጽ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣታቸውንም ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም