የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ
ባህርዳር ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ካርዳቸውን በመጠቀም ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን በባህርዳር ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ማህሌት በላይ በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ቀደም ሲል መውሰዳቸውን አውስተዋል።
በወሰዱት የምርጫ ካርድም የተጀመረውን ልማትና ዕድገት ያፋጥናል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተው ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ሀጂ አዲስ አብዱራህማን እንዳሉት ያለፉትን ሁሉንም ምርጫዎች በንቃት በመሳተፍ ይመራኛል የሚሉትን ፓርቲ መምረጣቸውን አስታውሰዋል።
በነገው እለት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫም በድምጻቸው የሚያምኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
''በወሰድኩት የምርጫ ካርድ ዴሞክራሲያዊ መብቴን ተጠቅሜ ሀገር ይመራል፣ ያስተዳድራል ብዬ ያመንኩበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ'' ያለው ደግሞ ወጣት ዘለዓለም አሸናፊ ነው።
''የወሰድኩትን ካርድ ይበጀኛል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበኩ እገኛለሁ'' ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።