ድምፃችን ዋጋ እንዳለው በመገንዘብ ነገን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ድምፃችን ዋጋ እንዳለው በመገንዘብ ነገን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ድምፃቸው ዋጋ እንዳለው በመገንዘብ በነገው ዕለት ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በካርዳቸው ነገን መወሰን የሚችሉበት በመሆኑ እለቱን በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አባገዳ ሰይፉ ከድር እንዳሉት ምርጫ የሚበጀንን መንግሥት ለመወሰን የሚያስችል በመሆኑ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ስንታየሁ ረና በበኩላቸው ድምፃቸው ዋጋ እንዳለው በመገንዘብ በነገው እለት ለመጪው ትውልድ የተሻለ የሚሰራ መንግሥትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ምርጫ በአምስት ዓመት አንዴ የሚገኝ ክስተት መሆኑን በመግለጽ፤ በድምፃችን መንግሥት የሚሆነንን የምንወስንበት ነው ያሉት ጥዑመልሳን አብርሃም በበኩላቸው ድምፃቸውን ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ዕለቷን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ኤልሳቤት ተፈራ፣ ሀሩን ንጉሴና አሚና ከማል በተለይ ወጣቱ ምርጫ የነገ መንግሥትን ለመመስረት የሚያስችል እድል መሆኑን በመገንዘብ ለስኬታማነቱ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።