ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከዛምቢያ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዋን ከዛምቢያ ጋር ታደርጋለች።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ትናንት በሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ብሩንዲን 2 ለ 1 በማሸነፍ በድምሩ ተጋጣሚውን 4 ለ 2 በመርታት ለመጨረሻው ዙር ማጣሪያ አልፏል።

በአሰልጣኝ ራውዳ አሊ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ዙር ጨዋታውን ከዛምቢያ ጋር እንደሚያደርግ ታውቋል።

የዛምቢያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሜዳው ውጪ ባደረገው የመልስ ጨዋታ 2 ለ 0 አሸንፏል።

በኪባሳ ማሊባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፒዳህ ሙዙዋ እና ኤልሳቤት ሞፍያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ዛምቢያ በድምር ውጤት 7 ለ 0 በማሸነፍ የመጨረሻውን ዙር ተቀላቅላለች።

ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ትጫወታለች።

ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎቿን በሰኔ ወር መጨረሻ እና ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ታደርጋለች።

10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም