ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለትውልዱ የሚበጅን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን አንድነት በማስጠበቅ ለትውልዱ የሚበጅን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን አንድነት በማስቀጠል ለትውልድ የሚበጅ ፓርቲን ለመምረጥ ዝግጁ ናቸው።

የመዲናዋ ነዋሪ ጌታቸው ረጋሳ፤ የሀገርን አንድነት በማስቀጠል ለነገው ትውልድ ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በነገው ዕለት ምርጫ በሚጀመርበት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ተገኝተው ለመምረጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የመራጭነት ካርዳቸውን በመጠቀም በማለዳ በመውጣት በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣት አብርሃም ለማ በበኩሉ፤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብሎ የሚያስበውን ፓርቲ በጠዋት ተነስቶ ለመምረጥ መዘጋጀቱን አረጋግጧል።

ወይዘሮ በለጡ መኩሪያ፤ በነገው እለት በሰዓቱ በመገኘት ለመምረጥ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም የመምረጥ  መብታቸውን መጠቀም እንዳለባቸው መክረዋል።

በአዲስ አበባ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በየምርጫ ጣቢያዎች በመሰራጨት ዝግጁ እየሆኑ ይገኛሉ። 

በአዲስ አበባ የምርጫ ክልል-16 የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ጌታቸው መኩሪያ፤ በምርጫ ጣቢያው የተመዘገቡ መራጮችን በሰዓቱ ማስተናገድ የሚያስችል የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።

በነገው ዕለት ከጠዋቱ 12 ሰዓት የድምፅ አሰጣጥ ሥነ-ስርዓቱን ለማስጀመር ዝግጁ ነን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም