ቀጥታ፡

በደገሀቡር ከተማ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በደገሀቡር ከተማ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አደም ኢብራሂም ገለጹ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መርሀግብር መሰረትም ለምርጫው አስፈላጊ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች በየምርጫ ጣቢያዎች ተሰራጭተዋል።

በሶማሌ ክልል ደገሀቡር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችም የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መሰራጨቱ ነው የተነገረው። 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ልዩ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ረዳት ኮሚሽነር አደም ኢብራሂም ፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። 

የዝግጅት ስራዎችም ቀደም ብለው መከናወናቸውን ተናግረዋል። 

ፖሊስ በቁሳቁስ ስርጭት ወቅት እጀባ በማድረግ በየምርጫ ጣቢያዎችም በቂ ጥበቃ በመመደብ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በነገው እለት ለሚካሄደው ምርጫ አስፈላጊው የፀጥታ ስራ ዝግጅት መጠናቀቁንም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም