በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሌሞ 01 ምርጫ ክልል ምርጫ ለማስፈጸም አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሌሞ 01 ምርጫ ክልል ምርጫ ለማስፈጸም አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል
ሆሳዕና፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ሌሞ - 01 ምርጫ ክልል በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ለማስፈጸም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ።
የምርጫ ክልሉ ሀላፊ አቶ ሙሉቀን አሻግሬ እንደገለፁት በምርጫ ክልሉ ለሚገኙ 140 የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ተሰራጭቷል።
የምርጫ ቁሶቹ ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች እንደተላኩና በምርጫ ጣቢያዎች እንደደረሱ መረጋገጡንም ተናግረዋል።፡
በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን ስኬታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።
በምርጫ ክልሉ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ስልጠና የወሰዱ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች ለነገው ምርጫ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
መራጮችም ነገ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎቹ ተገኝተው ድምጻቸውን እንዲሰጡ በጣቢያዎቹ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በሌሞ - 01 ምርጫ ክልል ሥር የሚገኘው ሆሳዕና ሄጦ ቀበሌ ጥምቀተ ባህር ፊት ለፊት ምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚ አለምፀሐይ ቦጋለ፣ በነገው እለት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያው ደርሶ የዝግጅት ሥራው መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።