ቀጥታ፡

በወልቂጤ ምርጫ ክልል ለጠቅላላ ምርጫው ሲደረግ የነበረው ዝግጅት ተጠናቋል

ወልቂጤ ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ምርጫ ክልል ለጠቅላላ ምርጫው ሲደረግ የነበረው ዝግጅት መጠናቀቁን የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ጀማል ገለጹ።

የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ አቶ ሲሳይ ጀማል፤ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 141 የምርጫ ጣቢያዎች  ድምጽ ለመስጠት የሚያስችሉ ግብዓቶች ተሟልተው ድምጽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የውሃ ልማት ሰፈር  ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ መኖር ግርማ፤ በምርጫ ጣቢያው የድምጽ አሰጣጡን ሂደት ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በጣቢያው የሚያስፈልጉ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች ተጠቃለው መድረሳቸውን ጠቅሰው፣ በነገው እለት ለመራጩ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ የድምጽ መስጫ ድንኳኖችና መቀመጫ ወንበሮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የእድገት በር ቦሎ መንደር ኪራይ ቤት ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ ወይዘሮ አለም ደስታ በበኩላቸው፤ ምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጫው ቀን ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

አስተባባሪው አክለውም፥ በድምጽ መስጫው እለት መራጩ ህዝብ ከዝናብና ከጸሃይ ተከልሎ ያለምንም እንግልት ድምጹን ለመስጠት የሚያስችለው ስፍራ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በምርጫ ጣቢያው ድንኳን ተደኩኖ ስፍራው ለመራጩ ህዝብ ምቹ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የመናኸሪያ ቀበሌ ወጣት ማእከል ምርጫ ጣቢያ ሃላፊ አቶ ብሩክ እሸቱ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም