በነቀምቴ እና ጊምቢ ምርጫ ክልሎች ለድምጽ መስጫ ሂደቱ ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ እና ጊምቢ ምርጫ ክልሎች ለድምጽ መስጫ ሂደቱ ዝግጅት ተጠናቋል
ነቀምቴ/ጊምቢ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በነቀምቴ እና በጊምቢ ምርጫ ክልሎች ለነገው የድምጽ መስጫ ሂደት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የምርጫ ክልሎቹ አስተባባሪዎች ገለጹ።
በሁለቱም የምርጫ ክልሎች የሚገኙ ጣቢያዎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶችን ተደራሽ በማድረግ መራጮችን ለመቀበል ተዘጋጅተዋል።
በነቀምቴ ምርጫ ክልል ስር በሚገኙ 108 የምርጫ ጣቢያዎች ነገ ከጠዋቱ 12:00 ጀምሮ ለሚካሄደው ምርጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ተሰራጭተው መጠናቀቃቸው ተገልጿል።
የምርጫ ጣቢያ ኃላፊው አቶ ቢሊሱማ አፈታ እንደገለጹት፤ ማህበረሰቡ በነፃነት ድምፁን መስጠት እንዲችል የመራጮች መቀመጫ፣ የመሰለፊያ ቦታ እና የድምፅ መስጫ ድንኳን ዝግጅት ተጠናቋል።
ሌላኛው የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ከበደ ፉፋ በበኩላቸው፤ በጣቢያው የተመዘገቡ መራጮች ያለምንም እንግልት ድምፅ እንዲሰጡ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በጊምቢ ምርጫ ክልል ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጮችን ለማስተናገድ በ84 ምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የክልሉ አስተባባሪ አቶ ከበደ በቀለ ገልጸዋል።
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ ሂደቱን በስኬት ለመወጣት ወሳኝ የሆኑት የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችም እስከ ምርጫ ጣቢያዎቹ ድረስ ተሰራጭተዋል ብለዋል።
በዚሁ ምርጫ ክልል የሚገኘው የሆሮ ምርጫ ጣቢያ ተወካይ አቶ መዝገቡ ፍቃዱ ፤ ለነገው ምርጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችና ድንኳኖች ተዘጋጅተው መጠናቀቃቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።