በጋምቤላ ከተማ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለነገው የድምፅ አሰጣጥ ዝግጁ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ከተማ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለነገው የድምፅ አሰጣጥ ዝግጁ ሆነዋል
ጋምቤላ ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ከተማ አስተዳድር ምርጫ ክልል የሚገኙ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ለነገው የድምፅ አሰጣጥ ስነ ስርአት የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ ልማት ደነቀ፤ በምርጫ ክልሉ በሚገኙት 52 የምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊው የምርጫ ቁሳቁስ የማሟላትና ምርጫ ጣቢያዎችን ለመራጮች ምቹ የማድረጉ ተግባር መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በምርጫ ጣቢያዎች ከማለዳ ጀምሮ የድምፅ አሰጣጡን ለመጀመር የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ምርጫ ክልል የ05 ቀበሌ የዞን 6 ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ደረጀ ሙለቱ፤ በምርጫ ጣቢያዎቹ ለድምጽ አሰጣጡ የተሟላ ዝግጅት ተደርጎ ተጠናቋል ብለዋል።
በመሆኑም ነገ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ የድምፅ አሰጣጡ የሚጀመር ይሆናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።