ቀጥታ፡

የቡልድግሉ ወረዳ ነዋሪዎች ነገ በማለዳ በምርጫ ጣቢያቸው ተገኝተው ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል

ቡልድግሉ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ነገ በማለዳው ካርድ ባወጣንበት የምርጫ ጣቢያ ተገኝተን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቡልድግሉ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በክልሉ በቡልድግሉ ምርጫ ክልል በሚገኙ 35 የምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጠት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ የማሰራጨት ተግባር ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁም ተገልጿል። 

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የነገውን ልዩ ዕለት ካርዳችንን በመጠቀም ድምፃችንን የሃገር ልማትና ዕድገትን አጠናክሮ ያስቀጥላል ለምንለው ፓርቲ በመስጠት እናሳልፋለን።

ነገ በማለዳው ካርድ ባወጣንበት የምርጫ ጣቢያ ተገኝተን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉም ነዋሪዎቹ አክለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አቡድ ኃሊፋ እና ወጣት ጣሪቅ አንዋር በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ ቀደም ብለው መያዛቸውን ተናግረዋል።

በነገው ዕለትም ለሚካሄደው የድምጽ አሰጣጥ መርሃ ግብር በማለዳው ተገኝተው ድምፃቸውን እንደሚሰጡም አረጋግጠዋል።

በምርጫው ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አብዱነቢር ሱሌማን ናቸው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቡልድግሉ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አህመድ ያሲን በበኩላቸው፤ በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 35 የምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጠት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

በምርጫ ክልሉ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ታዛቢዎቻቸውን በየምርጫ ጣቢያው ዝግጁ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም