የድምጽ መስጫ ቀኑን በጉጉት እየጠበቅን ነው - የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የድምጽ መስጫ ቀኑን በጉጉት እየጠበቅን ነው - የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች
አምቦ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመያዝ የድምጽ መስጫ ቀኑን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ነገ በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ፣ ሕገ-መንግሥቱ የሰጣቸውን መብት ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሶፊያ አለሙ እንዳሉት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ማንኛውም ካርድ የወሰደ ሰው በነገው ዕለት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በምርጫው ላይ ተሳትፎ ድምጽ መስጠት አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ወጣት ሰኚ ንጉሴ በበኩሉ፤ የምርጫ ካርድ ከወሰደበት ቀን ጀምሮ የአንድ ሰው ድምፅ ትልቅ ዋጋ እንዳለው በመረዳት ካርዱን በጥንቃቄ ይዞ መቆየቱን ተናግሯል።
ነገ በሚካሄደው ምርጫ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ቀኑን በጉጉት እየጠበቀ መሆኑንም አክሏል።
አቶ ብርሃኑ ሞጋሳ በበኩላቸው፤ በወሰዱት የመራጭነት ካርድ ለኢትዮጵያ እድገት ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙኃን ሲተላለፉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሮችንና የተለያዩ መረጃዎችን መነሻ በማድረግ የሚመርጡትን ፓርቲ መወሰናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።