ነገ በሌሊት ወጥተን ድምፃችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል- የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ነገ በሌሊት ወጥተን ድምፃችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል- የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች
ቦንጋ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ነገ በሌሊት ወጥተው ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
መራጮች የወሰዱትን ካርድ ተጠቅመው ለሀገሪቱ ልማትና እድገት ይሰራል ለሚሉት ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት ነገን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ይህንንም በተመለከተ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎችም ነገ በሌሊት ወጥተው ድምፃቸውን ለመስጠት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የወሰዱትን ካርድ በጥሩ ሁኔታ ይዘው መቆየታቸውን የገለፁት ወጣት አሰግድ ሳህሌና አቶ አብደላ አባገሮ የነገውን ቀን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነገ ለድምፅ መስጫው ቀደም ብለው በመገኘት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ለመምረጥ ተዘጋጅተን ግንቦት 24ን በጉጉት እየጠበቅን ነው ያሉት ወ/ሮ የምስራች ዳምጠው እና አቶ ታምሩ ገብረ ስላሴ ነገ ማልደው በመውጣት ድምፃቸውን እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
የምርጫ ካርዱ ዋጋ የሚኖረው ድምጽ ሲሰጥበት ብቻ በመሆኑ ሁሉም መራጭ ድምጹን ሳያባክን እንዲጠቀምም መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።