ቀጥታ፡

በባህር ዳር የምርጫ ክልል ለሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል

ባህር ዳር ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል በነገው ዕለት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል ሲሉ የምርጫ ክልሉ ሃላፊ ገለፁ።

ኃላፊው አቶ ሞላልኝ ደሳለው እንደገለፁት፤ በነገው ዕለት ለሚካሄደው ምርጫ በጥሩ ሁኔታ ዝግጅት ተደርጓል።

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ለድምፅ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።

የምርጫ ቁሳቁሶችንም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ስራ ከትናንት ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በነገው ዕለትም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ መራጩ ማህበረሰብ ተመዝግቦ ባወጣው ካርድ ድምፅ ይሰጣል ነው ያሉት።

በባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል 164 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ኃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም