ቀጥታ፡

የድሬዳዋ ነዋሪዎች በወሰዱት ካርድ የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል

ድሬዳዋ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በወሰዱት ካርድ ለሀገርን ለህዝብ የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ እየተጠባበቁ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የድሬደዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን የሰጡት የድሬደዋ አስተዳደር ነዋሪዎች እንደተናገሩት፤ ነገ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ከነዋሪዎቹ መካከል ኮማንደር ጀሬ ተርቼ፤ በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ያቀረቡት ክርክር የሚመርጡትን በአግባቡ ለመለየት አስችሏቸዋል።

ነገ ዕድሜያቸው ለመምረጥ ከደረሱት አምስት ቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር እና ለህዝብ አንድነት መጠናከር የተሻለ ሃሳብ ይዞ የቀረበን ፓርቲ ለመምረጥ እየተጠባበቁ መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ጋሻው ተሰማ እና አቶ መኪ ኡምሪክ በበኩላቸው፤ ለምርጫ ባወጡት ካርድ ነገ ለሚፈልጉት ፓርቲ ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ  ድምፅ ለመስጠት እየተጠባበቁ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የተለያዩ ቁሶችን ተዘዋውረው በመሸጥ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት አቶ አባስ አሊይ ናቸው።

በወሰዱት ካርድ ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማት እና ለህዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን በመጠቆም።

ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ  ዜጋ ሁሉ ያወጣውን ካርድ  በምርጫው በመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አቶ አባስ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም