ቀጥታ፡

የመራጭነት ካርዳችንን ለሀገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ይሁንታ እንቸርበታለን - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በነገው ዕለት ለሀገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ይሁንታ እንደሚቸሩበት ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በነገው ዕለት የሚካሄደውን ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀናል የሚሉትን አካል ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።

በዚህም የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በነገው ዕለት በጠዋት በመውጣት ለሀገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ይሁንታ እንደሚቸሩበት ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ካሚል አህመዲን ቀደም ብሎ የምርጫ ካርድ በዲጂታል ስርዓት መውሰዳቸውን ገልጸው፤  በነገው እለት የሚካሄደውን ምርጫ በጠዋት በምርጫ ጣቢያ በመገኘት ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የምርጫ ጊዜው ከመድረሱ በፊት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጭ ሲያካሂዱት የነበረውን የምርጫ ክርክር ማን ለሀገር ቀጣይ እድገት ይሰራል የሚለውን እንድንለይ ጠቅሞናል ብለዋል። 

በዚህም ለሀገርና ለህዝብ ይጠቅማል ብዬ ያመንኩበት ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መስፍን ገዛሀኝ በበኩላቸው፤ የሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት የምርጫ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ቅድመ ዝግጅታቸውን ቀደም ብለው እንዳጠናቀቁ ገልፀዋል።

በዚህም ለሀገር እድገት ይሰራል፤ ይሆነኛል ብለው ያመኑትን ፓርቲ  ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ምርጫ ለአንዲት ሀገር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመረዳት እና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ይረዳቸው ዘንድ የምርጫ ካርድ ቀደም ብለው በመውሰድ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ዳዊት ዱባለ ናቸው።

በዚህም የወሰዱትን ካርድ በመጠቀም ይሆነኛል የሚሉትን ፓርቲ ነገ በጠዋት ምርጫ ጣቢያ በመገኘት ለመምረጥ በጉጉት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ታደሰ ብርሃኑ በበኩላቸው ነገ በጠዋት ተገኝተው ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም