በባሌ ዞን የተለያዩ የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የተለያዩ የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል
ሮቤ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን በሚገኙ የተለያዩ የገጠር ወረዳዎች የምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎችና ታዛቢዎች ገለጹ።
በዞኑ የሚገኙት የጎባ፣ ዲንሾና ሲናና ወረዳዎች ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መሟላታቸውንና ሂደቱን የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎችና ታዛቢዎች በቦታው ተገኝተው እየታዘቡ መሆናቸው ተገልጿል።
በጎባ ወረዳ የወልተኢ ማግዳ ምስራ ገጠር ቀበሌ የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ወይዘሮ ፋንቱ አበራ፤ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በጣቢያው ሙሉ በሙሉ መሟላታቸውን ተናግረዋል።
በዚሁ የምስራ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ የሆኑት አቶ አሚኖ አማን በበኩላቸው እስከ አሁን ያለው ሂደት በምርጫ ጣቢያው ከተመደቡ አስተባባሪዎችና ሌሎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በተመሳሳይ በዲንሾ ወረዳ የሆማ ቀበሌ የምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሙሂዲን ኢድሪስ፤ በጣቢያው ለምርጫው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መሟላታቸውንና የተመደቡ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዲንሾ ወረዳ የሆማ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ የሆኑት ወይዘሮ ከዲጃ ማማ በሰጡት አስተያየትም፤ ለነገው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች በህጉ መሰረት እየተመሩ መሆኑን መታዘባቸውን አረጋግጠዋል።
በዞኑ በተመረጡ ወረዳዎች የተደረገው ምልከታ እንደሚያሳየው፥ የምርጫ ጣቢያዎቹ ለነገው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ አጠናቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።