ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ለምርጫው እለት የድምጽ መስጫ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል

አዳማ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ ለምርጫው እለት መራጮችን ማስተናገድ የሚያስችሉ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውን የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች አስታወቁ።

የኢዜአ ሪፖርተሮች በአዳማ ከተማ ተዘዋውረው በተመለከቷቸው በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የድንኳን ተከላና የሚስጥር ድምጽ መስጫ ቦታዎች ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።

ምልከታ ከተደረገባቸው መካከል የአንዶዴ ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሳፊ አሺም፤ በምርጫ ጣቢያው የድምጽ አሰጣጡን ሂደት ስኬታማና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። 

በጣቢያው የሚያስፈልጉ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች ተጠቃለው መድረሳቸውን ጠቅሰው፣ለመራጩ አመቺ በሆነ ቦታ ላይ የድምጽ መስጫ ድንኳኖችና መቀመጫ ወንበሮች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአዳማ ከተማ የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ መለሰ አዱኛ፤ ምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጫው ቀን ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

የሚስጥር ድምጽ መስጫ ሳጥኖችን ጨምሮ የተለያዩ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።

አስተባባሪው አክለውም፣ በድምጽ መስጫ እለቱ መራጩ ህዝብ ያለምንም እንግልት ድምጹን መስጠት የሚያስችለው ስፍራ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

የሁንዳኦል ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ሙላቱ አለማየሁ በበኩላቸው፤ በጣቢያው ድንኳን መዘጋጀቱንና ስፍራው ምቹ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም