ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት እየተጠባበቅን ነው - አካል ጉዳተኞች 

ሐረር ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦  ነገ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት እየተጠባበቁ መሆኑን በሐረር ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አካል ጉዳተኞች ያለምንም እንቅፋት መራጭነታቸውን እንዲያረጋግጡና ድምፅ እንዲሰጡ የሚያስችሉ መመሪያዎችንና አሠራሮችን ሲዘረጋ ቆይቷል።

በሐረር ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በነገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ያላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት ይኸው የአካታችነት ጥረት ውጤት መሆኑን ያሳያል። 

በከተማው ካነጋገርናቸው መራጮች መካከል ሽመልስ ሽፈራው "ዓይነ ስውርነት ሳይገድበኝ ህገ መንግስታዊ  የመምረጥ መብቴን በመጠቀም  የምርጫ ካርድ አስቀድሜ ወስጃለሁ" ሲል ነው የተናገረው።

"በተለይም የአካል ጉዳተኞችን መብት የሚያስጠብቅና ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብዬ የማምንበትን ፓርቲ እመርጣለሁ"' ሲል ተናግሯል።

በዘንድሮው የምርጫ ሂደት ለአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ የተሰጠው ልዩ ትኩረት እጅግ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ደግሞ  አቶ ኢምራን አህመድ ናቸው።

ይህም የአካል ጉዳተኞችን እኩል ተሳታፊነትን  የማረጋገጥ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በዘንድሮም ምርጫ የምርጫ ካርድ አስቀድሜ ወስጃለሁ ያሉት አቶ ኢምራን "ነገ በጠዋት ተነስቼ  ይበጀኛል፣ ይሆነኛል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለው" ብለዋል።

ሁሉም ነዋሪ በነቂስ ወጥቶ የሚወክለውን ፓርቲ እንዲመርጥም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም