ቀጥታ፡

ኡሁሩ ኬንያታ በጠቅላላ ምርጫው ዝግጅት ዙሪያ ከአፍሪካ ዲፕሎማቶች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ ኡሁሩ ኬንያታ፣ በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ዙሪያ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ጋር ዛሬ መክረዋል።

ውይይቱ ጠቅላላ ምርጫውን ስኬታማ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አመልክቷል።

ለዚህ ታሪካዊ ሂደት ህብረቱ ከ37 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 73 አባላትን ያቀፈ ታዛቢ ቡድን አሰማርቷል።


 

በልዑኩ ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የምርጫ ባለሙያዎች የተካተቱ ሲሆን፣ ስብጥሩም ህብረቱ ለአካታችነትና ለስርዓተ-ፆታ እኩልነት የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።

ከታዛቢዎቹ መካከል 61 በመቶው ሴቶች ናቸው።

የታዛቢ ቡድኑ ከመደበኛው ድምፅ መስጠት ሂደት አስቀድሞ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተከናወኑትን የመጨረሻ ምዕራፍ የዝግጅት ስራዎች ሲገመግም ቆይቷል።

ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት ይህ አጠቃላይ ምርጫ፣ የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ጉዞ የሚያሳድግ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ ተወስዷል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።


 

በኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው ይህ ልዑክ የምርጫውን ሂደት በግልፅነት፣ በፍትሃዊነትና በተዓማኒነት መርህ ለመታዘብ በመላ ሀገሪቱ ተሰማርቷል።

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች መገኘት አህጉሪቱ በራሷ ዲሞክራሲያዊ ሂደቶች ላይ ያላትን ሚና የሚያሳይ ነው።

ይህ ተልዕኮ በአፍሪካ ዲሞክራሲ ውስጥ የታየ ትልቅ መዋቅራዊ ለውጥ ነው፤ እንደ አፍሪካ ህብረት ያሉ ተቋማት በአባል ሀገራት ምርጫዎችን በመገምገም እና በማጠናከር ረገድ መሪነቱን እየወሰዱ መሆኑንም ያረጋግጣል።

አሰራሩ በአህጉሪቱ የምርጫ ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ፣ የተቋማትን አመኔታ የሚገነባ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም