ቀጥታ፡

በምርጫው ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል-የሸቤ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን የሸቤ ከተማ ነዋሪዎች ነገ በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በማለዳ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ይካሄዳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሸቤ ሶምቦ ወረዳ የሸቤ ከተማ ነዋሪዎች ነገ ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና ነገ በማለዳ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሰይፉ አባቦልጉ እንደተናገሩት፤ የምርጫ ካርዳቸውን በወቅቱ ወስደው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው፤ ነገ በማለዳ በመውጣት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ወጣት አብዱሰመድ ሃይሌ በበኩሉ፤ ምርጫው ይበጀናል የምንለውን ለመምረጥ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቅን እንገኛለን ሲል ገልጿል።

የምርጫው ሂደት ፍጹም ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ጋሊ ከድር እንዳለው፥ ለሀገርና ለአካባቢው ዕድገት ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በማለዳ በመውጣት ድምጻቸውን ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ያረጋገጡት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ አይሻ አባዱራ ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም