ለሀገር ይበጃል ለምንለው አካል ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል -የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ይበጃል ለምንለው አካል ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል -የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች
አዳማ ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ ነገ በሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል ለምንለው አካል ድምጽ ለመስጠት ተዘጋጅተናል ሲሉ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የአዳማ ከተማ ነዋሪ አቶ ፉዓድ ነጋሽ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ቀደም ብለው የምርጫ ካርድ ወስደው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
"ይወክለኛል፣ ለሀገር ይበጃል የምንለውን አካል ለመምረጥ ተዘጋጅተናል" ያሉት አቶ ፉዓድ፤ በዚህም የሚፈልጉትን በካርዳቸው እንደሚወስኑ ገልጸዋል።
የሚፈልጉትን አካል በካርዳቸው በመወሰን ፍላጎታቸውን እውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ለሀገር የሚበጀውን አካል ለመምረጥ የነገዋን ዕለት በጉጉት እየጠበቁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሲሳይ ኢብሣ ናቸው።
በነገው ዕለት በሚካሄደው ምርጫ ይጠቅመናል ያሉትን ፓርቲ በነፃነትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመምረጥ ካርዳቸውን ይዘው እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ እመቤት ታደሰ በበኩላቸው፤ በምርጫው ለመሳተፍና ድምፅ ለመስጠት ካርዳቸውን አዘጋጅተው የነገውን ዕለት እየጠበቁ ይገኛሉ።
በነገው ዕለት ወጣቶችን የሚጠቅም ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ ወጣት ጀዋር ኦብሴ ሲሆን ለሀገር ይበጃል ለምለው አካል ድምጽ እሰጣለሁ ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።