ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የምርጫ ጣቢያዎች የተሟላ ዝግጅት አድርገዋል

ጎንደር ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ ለድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ምርጫ ጣቢያዎች የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪዎች ገለጹ፡፡

በከተማዋ በሁለት የምርጫ ክልሎች የተቋቋሙ 240 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው አስፈፃሚዎችም ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።

በከተማው የጻዲቁ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ላቀው ወረታ፤ በምርጫ ጣቢያው የምርጫ ቁሳቁሶችን ተረክበን ለምርጫው ዝግጁ ሆነን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።

በምርጫ ጣቢያው የመራጮች የሚስጥር ድምጽ መስጫ ልዩ ክፍሎችን ጨምሮ የተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የምርጫ ታዛቢዎች እንዲሁም ለምርጫ አስፈፃሚዎች ዝግጁ ሆኗል ብለዋል። 

በመሆኑም በነገው እለት ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ የድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርአቱን ለመጀመር የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የኮረፌ ተራ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ዳዊት ንጉሱ፤ በምርጫ ጣቢያው የምርጫ ቁሳቁሶች የተሟሉ መሆኑንና ለድምፅ አሰጣጡ የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ የቀበሌ 6 ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ዋሴ፤ በድምጽ መስጫው እለት ድምጽ ሰጪዎች እንዳይጉላሉ ምርጫ ጣቢያዎች ምቹ ሆነው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ የምርጫ ጣቢያዎች ለመራጮች ክፍት ሆነው የሚጠብቁ በመሆኑ ዜጎች ካርዳቸውን በመያዝ የሚስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም