በጅማ እና በነገሌ ቦረና የምርጫ ክልሎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ እና በነገሌ ቦረና የምርጫ ክልሎች ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል
በጅማ እና ነገሌ ቦረና ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በጅማ እና በነገሌ ቦረና ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት በሙሉ መጠናቀቁን የምርጫ ክልሎቹ ጽሕፈት ቤቶች ገለጹ።
የነገሌ ምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ አባይነህ ወርቁ እንደገለጹት፤ በምርጫ ክልሉ በሚገኙ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች አስፈላጊ የሆኑ የምርጫ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ ደርሰዋል።
የምርጫ ሂደቱን በታማኝነትና በገለልተኝነት የሚያስፈጽሙ ከ1 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች በየጣቢያዎቻቸው መሰማራታቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለምርጫው የሚያስፈልጉ ድንኳኖች ተጥለዋል፤ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች የተሟሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለጠቅላላ ምርጫው በነገሌ ምርጫ ክልል ሥር በሚገኙ 5 ወረዳዎች ውስጥ መራጮች ድምፅ የሚሰጡባቸው 167 ምርጫ ጣቢያዎች መቋቋማቸው ተገልጿል።
የየጣቢያዎቹ አስተባባሪዎች ምርጫውን በስኬት ለመምራት ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
የሀሎ ጋፍትሮ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ አጥናፉ ዓለማየሁ ከ6 የምርጫ አስፈጻሚ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን መራጮችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለምርጫው ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ቁሳቁሶች በሙሉ እንደታሸጉ ትላንት ከሰዓት በኋላ ጣቢያው እንደደረሱ አስታውቀዋል።
ሌላው የመድኃኒት ፈንድ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ አብዱላሂ ጡሩ፤ የምርጫ ቁሳቁሶች ከትላንት ጀምሮ መጓጓዛቸውንና ጣቢያቸው መድረሱን ተናግረዋል።
"ነገ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ መራጮችን ለመቀበል ሁሉንም ዝግጅት አጠናቀን እየተጠባበቅን ነው" ብለዋል።
ሁሉም የምርጫ አስፈጻሚዎች በጣቢያቸው መገኘታቸውን ጠቁመው፤ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንዲሆን መራጮችን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኦጎባ ምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ጉዮ አፈቱ ናቸው።
በተመሳሳይ በጅማ ከተማ በሁሉም የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት መጠናቀቁን የከተማዋ ምርጫ ክልል ኃላፊ ነቢያት አብርሃም ገልጸዋል።
በጅማ ከተማ የቁሳቁስ ስርጭቱ መጠናቀቁን ገልጸው የምርጫ ጣቢያዎችም በጥሩ ዝግጅት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።