በድሬደዋ አስተዳደር ለሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ አስተዳደር ለሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል
ድሬደዋ፣ ግንቦት 23/2018(ኢዜአ)፡- በድሬደዋ አስተዳደር ነገ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን እንደተናገሩት፤ በአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች ለሚገኙ 130 የምርጫ ጣቢያዎች ለድምፅ አሰጣጡ የሚያስፈልጉ ቁሶች ትናንት በስኬት ተሰራጭተዋል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ በከተማው ለሚገኙ 167 ምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ቁሶችን የማጓጓዙ ስራ በስኬት መካሄዱን ተናግረዋል።
አቶ ዚያድ አክለውም በየምርጫ ጣቢያዎቹ ስለ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት ስልጠና የተሰጣቸው ታዛቢዎች መመደባቸውን ጠቅሰው የድምፅ መስጫ ስፍራዎችም ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጭ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ነገ በአስተዳደሩ ለሚካሄደው የድምፅ አሰጣጥ አስፈላጊው የቅደመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የድሬደዋ ምርጫ ክልል አንድ ኃላፊ አቶ ከድር ሱልጣን በበኩላቸው ትናንት ለገጠር ምርጫ ጣቢያዎች የተላኩት የምርጫ ቁሶች ያለምንም ችግር መድረሳቸውን አንስተዋል።
በዛሬው ዕለት ደግሞ በከተማዋ ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከማለዳው ጀምሮ በስኬት መጓጓዛቸውን ገልጸዋል።