የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በመራጭነት ካርዳቸው ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በመራጭነት ካርዳቸው ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የመራጭነት ካርዳቸውን በመጠቀም መንግሥት የሚመሰርቱበትን ፓርቲ ለመምረጥ ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገለጹ።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።
ዜጎችም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚበጃቸውን መርጠው መንግሥታቸውን ለመመስረት የነገዋን ጠዋት 12 ሰዓት በጉጉት እየጠበቁ ይገኛል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በመጠቀም መንግሥት የምንመሰርትበት ታሪካዊ መድረክ ነው።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ማማሩ ዘላለም፤ ምርጫ የሀገርን ዕድገትና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመስረቻ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀም ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት ነገን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያንም የመራጭነት ካርድ በወሰዱባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ነገ በጠዋት በመገኘት ለሀገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ይሰራል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ዮሐንስ አቡሀይ በበኩላቸው፤ የምርጫ ካርድ አውጥተናል፣ ነገ በጠዋት ድምፃችንን እንሰጣለን ብለዋል።
ሁሉም ሰው በነቂስ ወጥቶ የሚጠቅመውን መምረጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አቶ ኑር ታፈሰ ፤ ያስተዳድረናል የተሻለ ነገን ይፈጥርልናል ያልነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ወጣት ሜላት ምናየ በበኩሏ፤ ድምፄ ለመንግሥት ምስረታ ወሳኝ በመሆኑ በምርጫ ጣቢያ በማለዳ በመገኘት ለኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚነት ለሚሰራ ፓርቲ ድምፄን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ብላለች።
ወጣት በላይነሽ ታደለ በአስተያየቷ፤ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጥ የፖለቲካ ፓርቲ ነገ በጠዋት ተነስታ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀቷን ተናግራለች።