የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ ነዋሪዎች ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2018(ኢዜአ)፦በሸገር ከተማ የየካ ጣፎ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት የምርጫ ካርድ ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገለጹ።
ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን አስታውቋል።
በሸገር ከተማ የየካ ጣፎ ክፍለ ከተማ ኢዜአ ተዘዋውሮ ያነጋራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ምርጫ የአንድ ሀገር የሰለጠነ ፖለቲካዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንቢያ መሳሪያ ነው።
በዚህም ነገ ሰኞ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ከማለዳው ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለሚበጃቸው ፓርቲ ድምፅ እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።
የክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ሶፍያ አሕመድ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ በማውጣት ዕለቱን እየተጣበበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ነገ ሰኞ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በማለዳ በመነሳት ለሀገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ይበጃል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ በመስጠት እንደሚመርጡ ተናግረዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ያሲን መሐመድ በበኩላቸው፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ዕለቷን በጉጉት እየተጠባበቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
በጠቅላላ ምርጫው ሂደት ላይ በወሰዱት የመራጭነት ካርድ በዕለቱ ደምፅ እሰጣለው ያሉት ደግሞ የክፍለ ከተማው ነዋሪ ሽብሩ ደረጄ ናቸው።
ኢትዮጵዊያንም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የወሰዱትን የምርጫ ካርድ በመጠቀም ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢሳያስ ማሞ በበኩላቸው፤ በማለዳ በመውጣት በወሰዱት የመራጭነት ካርድ ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።