በዳራ እና አለታወንዶ ምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዳራ እና አለታወንዶ ምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ነው
አለታ ወንዶ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦በደቡባዊ ሲዳማ ዞን ሥር ባሉ ዳራ እና አለታወንዶ ምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው።
የዳራ ምርጫ ክልል አስተባባሪ ወይዘሮ ራሔል ወርቅአገኘሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምርጫ ቁሳቁሱ እየተሰራጨ ያለው በምርጫ ክልሉ ስር ለሚገኙ 88 የምርጫ ጣቢያዎች ነው።
የምርጫ ቁሶቹ ከትናንት ጀምሮ እየተሰራጩ መሆናቸውን ገልጸው፣ በዚህም የድምጽ መስጫ ሳጥንና ወረቀቶች፣ መከለያዎች፣ መዝገቦች፣ የጽህፈት መሳሪያዎችና ሌሎችም ለምርጫው አስፈላጊ የሆኑ ቁሶች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እየተሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአለታ ወንዶ ምርጫ ክልል ስር ለሚገኙ 112 ምርጫ ጣቢያዎችም የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ይገኛል።
በነገው እለት ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫም በአለታ ወንዶ ከተማ በምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ መስጫ የሚሆን የድንኳን ተከላና ሌሎችም አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።