የሲቪክ ማህበራት በባሌ ዞን በሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን በስፍራው ተገኝተው መታዘብ ጀምረዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪክ ማህበራት በባሌ ዞን በሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደቱን በስፍራው ተገኝተው መታዘብ ጀምረዋል
ሮቤ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች የሲቪክ ማህበራት ታዛቢዎች በቦታው ተገኝተው፣ የምርጫ ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ በቅርበት እየታዘቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ታዛቢዎቹ የምርጫ ቁሶች በየጣቢያዎቹ መሟላታቸውን እንዲሁም ለድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች በህጉ መሰረት እየተመሩ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል።
በሮቤ ከተማ ጎባ ክፍለ ከተማ እድር ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ የሆኑት አቶ ደምሴ በቀለ በሰጡት አስተያየት፤ በተመደቡበት የምርጫ ጣቢያ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ መሟላታቸውን መታዘባቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ምልከታቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች ለታዛቢዎች አስፈላጊውን መረጃና ትብብር እያደረጉላቸው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደምሴ፤ ሂደቱ ግልጽና ህጋዊ አሰራርን የተከተለ ሆኖ መቀጠሉን አመልክተዋል።
በጣቢያዎቹ ለመራጮች ድምፅ መስጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በሙሉ መሟላታቸውንና መራጩን ህዝብ እየተጠባበቁ መሆኑን በተግባር መታዘባቸውን የገለጹት ደግሞ በክፍለ ከተማው በኡርጂ በሪሳ የምርጫ ጣቢያ ሂደቱን በቅርበት እየታዘቡ የሚገኙት አቶ ብርሃኑ አዱኛ ናቸው።
እስካሁን ባለው ሂደት አጠቃላይ ተግባራቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳና መመሪያ መሰረት በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን በምልከታቸው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
በሮቤ ከተማ የሚገኘው የጨፌ ሆራ ቀበሌ የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ፈቂ ሐጅ ከድር ፤ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ መድረሳቸውንና አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሲናና ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ ተሾመ አሰፋ እንደገለጹት፤ በምርጫ ክልሉ ስር ለተደራጁ 106 የምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁስ የማሰራጨቱ ተግባር መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።
በምርጫ ክልሉ ስር በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የታዛቢዎች ምደባ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱንም አስታውሰዋል።
ህጋዊ እውቅና ያላቸው የሲቪክ ማህበራት አባላትና የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የላኳቸው ታዛቢዎች በነጻነት ምልከታቸውን እያደረጉ መሆኑንም አስተባባሪው ጠቁመዋል።
በባሌ ዞን በሚገኙ ሌሎች የምርጫ ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ታዛቢዎች ሙሉ በሙሉ በስራ ላይ እንደሚገኙና አጠቃላይ ሂደቱን የመታዘብ ስራቸው ተጠናክሮ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።