ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል 

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ነገ በሚካሄደው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ማልደው በመነሳት ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በጠዋቱ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

ወጣት አዲስ ይዘንጋው፤ የሀገርን ሁለንትናዊ ዕድገትና የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብሎ ያመነበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቷል።

በዚህም ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ መውሰዱን እና ነገ በማለዳ በመነሳት በምርጫ ጣቢያ ተገኝቶ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀቱን አረጋግጧል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ውዴ ሁነኛው በበኩላቸው፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ በትጋት ይሰራል ብለው ለሚያምኑት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም ነገ  በማለዳ በመነሳት ጎረቤትና ልጆቻቸውን በማስተባበር ጭምር የመራጭነት ካርድ በወሰዱበት የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሳታፊና በዲጂታል ሥርዓት የታገዘ ቀልጣፋ የመራጭነት ካርድ የማውጣት አገልግሎት የተሰጠበት ነው ያሉት ደግሞ አቶ አይሮ አወል ናቸው።

በዚህም ነገ በጠዋት በመነሳት ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን ድምፅ በሚሰጡበት የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው የሚወክላቸውንና ሀገርን ይጠቅማል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።

ለምለም አማረ በበኩላቸው፤ ነገ በማለዳ በመነሳት የመራጭነት ካርድ በወሰዱበት የምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም