ቀጥታ፡

በአዳማ ምርጫ ክልል አንድ፣ ሁለት እና ሦስት የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭት ተጠናቋል

አዳማ ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦ በአዳማ ምርጫ ክልል አንድ፤ ሁለት እና ሦስት የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭት ተጠናቆ ምርጫ ጣቢያዎችን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የምርጫ ክልሎቹ አስተባባሪዎች ገለጹ።

የአዳማ ምርጫ ክልል አንድ አስተባባሪ አቶ ደበሌ ወርቁ፣ በምርጫ ክልሉ ሥር በሚገኙ 202 ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ተሰራጭተዋል ብለዋል።

የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭቱ ትናንት መጠናቀቁን የገለጹት አስተባባሪው፤ የስርጭት ሂደቱ የተሳካ እንደነበርም አስረድተዋል።

የአዳማ ምርጫ ክልል ሁለት አስተባባሪ አቶ መኮንን ሲሳይ እንደገለጹት፤ በአዳማ ምርጫ ክልል ሁለት 115 የምርጫ ጣቢያዎች አሉ።

በክልሉ ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 28 የሚሆኑት በአዳማ ወረዳ ሥር የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፤ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ ስርጭቱን ትናንት ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል።

በተመሳሳይ በአዳማ ምርጫ ክልል ሦስት የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ስርጭት በ57 የምርጫ ጣቢያዎች መድረሱን የገለጹት ደግሞ የምርጫ ክልሉ አስተባባሪ አቶ አበበ ከሚሶ ናቸው።

በምርጫ ክልሎች ሥር የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎችን ለመራጮች ምቹ የማድረግ ሥራ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም