ቀጥታ፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል

አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 23/2018 (ኢዜአ)፦የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን ቀን እየተጠባበቁ ነው።

ኢዜአ በአርባ ምንጭ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ነገ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ድምጻቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጎአ ጉንኤ ባለቤታቸው እና ዕድሜያቸው ለመምረጥ የደረሱ ልጆቻቸውን ጨምሮ የምርጫ ካርድ ወስደው ድምጻቸውን ለመስጠት የነገውን የምርጫ ቀን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ምርጫ ሀገርን ከማጽናት ባለፈ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠልና ለቀጣይ ሀገር የሚመራን ፓርቲ ለመወሰን እድል ስለሚሰጥ ካርዴን ሳላባክን እጠቀምበታለሁ ብለዋል። 

በነገው እለት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል፤ ልማትንም ያፋጥናል ለምለው ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት ቀኑን እየጠበኩ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ሻናፎ አርሞ የተባሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ናቸው። 

ምርጫ በሀገር መጻኢ ዕድል ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ስላለው ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል።

ሌላኛዋ ወጣት ሕይወት በለጠ በበኩሏ በሀገር እጣፈንታ ላይ የሚወሰንበት ታላቅ ታሪካዊ ኩነት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ ዕድል በማግኘቷ መደሰቷን ተናግራለች።

በምርጫ ሂደት አንድ ድምፅ ዋጋ አለው ያለችው ወጣቷ የምርጫ ካርዷ እንዳይባክን በነገው እለት ይሆነኛል ለምትለው ፓርቲ ድምጿን በመስጠት ታሪካዊ አሻራዋን ለማሰረፍ መዘጋጀቷን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነገ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም