ቀጥታ፡

ፒኤስጂ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለተከታታይ ጊዜ አነሳ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ፒኤስጂ አርሰናልን በመለያ ምት  አሸንፏል።

ማምሻውን በሀንጋሪ ቡዳፔስት በሚገኘው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካይ ሃቫርትዝ በስድስተኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል አርሰናል መሪ ሆኗል።

የፒኤስጂው አምበል ማርኪኒዮስ ስህተት
ለሃቫርትዝ ግብ መቆጠር ምክንያት ሆኗል።

ከእረፍት መልስ ኡስማን ዴምቤሌ በ65ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ ላይ ባሳረፈው ጎል ፒኤስጂ አቻ መሆን ችሏል።

የወቅቱ የባለንዶር አሸናፊ ዴምቤሌ ዘንድሮ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ስምንት አድርሷል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ ምክንያት 30 ደቂቃ ተጨምሯል።

በጭማሪ ሰዓት ግብ ባለመቆጠሩ ምክንያት ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቷል።

ፒኤስጂ በመለያ ምት 4 ለ 3 በማሸነፍ ለተከታታይ የውድድር ዓመት የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ አንስቷል። የአውሮፓ ክብሩን አስጠብቋል።

የፓሪሱ ክለብ ከሪያል ማድሪድ በኋላ ለተከታታይ ዓመት ዋንጫውን ያነሳ ቡድን ሆኗል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የማንሳት ህልሙ አልተሳካም።

አርሰናል ከፕሪሚየር ሊጉ ድል በኋላ ድርብ ስኬት ማሳካት አልቻለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም