ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጤና አህጉራዊ መፍትሄ ለማምጣት ከማህበሩ ጋር ትሰራለች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ የፓን አፍሪካ ኤች.አይ.ቪ ክሊኒሻኖች ማህበር መመስረትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጤና አህጉራዊ መፍትሄ ለማምጣት ከማህበሩ ጋር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ። 

የፓን አፍሪካ የኤች.አይ.ቪ ክሊኒሻኖች ማኅበር ለሁለት ቀናት የሚቆይ የምስረታ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት፤ የኤች.አይ.ቪ በሽታ በዜጎች ህይወት ላይ የሚያሳድረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መከላከል የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍን የኤች.አይ.ቪ በሽታ ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት እንደተመዘገበባቸው ገልጸዋል።

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

 

የኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ሥርዓት ግንባታም የኤች.አይ.ቪ በሽታን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ ውጤታማነት በማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለኤች.አይ.ቪ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ውጤታማነት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የጤና ሙያተኞች፣ የልማት አጋሮችና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ድርሻ እንደነበራቸው አንስተዋል።

በበሽታው የተያዙ ዜጎችን የማህበራዊና ኢኮኖሚያ ተፅዕኖና ተጋላጭነት ለመቀነስ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የፓን አፍሪካ የኤች.አይ.ቪ ክሊኒሻኖች ማኅበር መመስረት የአህጉሪቱን ዜጎች የጤና ተጋላጭነት ችግሮች በሳይንሳዊ ምርምር መፍትሔ ለመስጠት ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንዳለበት አስገንዝዋበዋል።

የማኅበሩ ምስረታም የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ በማህበረሰብ ጤና ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል።


 

የፓን አፍሪካ የኤች.አይ.ቪ ክሊኒሻኖች ማኅበር ሊቀመንበር ዶክተር ሙሃንግዊ ሙላውዲዚ፤ ማኅበሩ የአህጉሪቱን ዜጎች የኤች.አይ.ቪ በሽታ ተጋላጭነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይም በሽታው በዜጎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ እንዲወሰድ በዓለም አቀፍ መድረክ ጭምር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ሀገራትም የዜጎችን የኤች.አይ.ቪ በሽታ ተጋላጭነት መቀነስ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ በመውሰድ የጋራ ትብብርን ማጠናከር እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም