የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ መድን እና መቀሌ 70 እንደርታ ከባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ኢትዮጵያ መድን አንድ አቻ ተለያይተዋል።
የወልዋሎው ጌቱ ኃይለማርያም በሰባተኛው ደቂቃ በራሱ መረብ ላይ ያስቆጠረው ግብ ኢትዮጵያ መድንን መሪ ሆኗል።
የኢትዮጵያ መድኑ ጋናዊ ተጫዋች እስማኤል አብዱልጋኒዩ በ12ኛው ደቂቃ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ወልዋሎ አቻ መሆን ችሏል።
ውጤቱን ተከትሎ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ41 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ43 ነጥብ ደረጃውን ከ13ኛ ወደ 12ኛ ከፍ አድርጓል። መድን ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር መቀሌ 70 እንደርታ እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
መቀሌ 70 እንደርታ በ35 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በ46 ነጥብ ከነበረበት 9ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ከፍ ብሏል።
‘
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች አቻ የወጣ (19 ጊዜ) ቡድን ነው።
ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን 1 ለ 0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል።
በዝናብ ምክንያት ዛሬ ከቆመበት ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ተጠናቋል።
ፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር በምታደርጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች ምክንያት የሚቋረጥ ሲሆን፣ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በ35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ይመለሳል።