ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ አለፈ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ2026 ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ ብሩንዲን 2 ለ 1 አሸንፋለች።

በኢንትዋሪ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ዳንሲል ኢራንዚ በስምንተኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል ብሩንዲን መሪ ሆናለች።

ምኅረት አየለ በ53ኛው እና ሊዲያ እያሱ በ73ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፏቸው ግቦች ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል።

ሊዲያ እያሱ በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለት ግቦችን ማስቆጠሯ የሚታወስ ነው።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ብሩንዲን 4 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ዓለም ዋንጫው የመጨረሻ ዙር ማጣሪያ አልፋለች።




ኢትዮጵያ በመጨረሻው ዙር ከዛምቢያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ዛምቢያ 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፋለች።

የሀገራቱ የመልስ ጨዋታ ነገ ይደረጋል።

ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎችን በሰኔ ወር መጨረሻ እና ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ታደርጋለች።

10ኛው የፊፋ የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። ቀሪ አራት ሀገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም