በሶማሌ ክልል ደገሀቡር ከተማ የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ደገሀቡር ከተማ የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ደገሀቡር ከተማ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ይገኛል፡፡
የደገሀቡር የምርጫ ክልል የሎጅስቲክስ ሀላፊ አብዱልህፈታህ መሀሙድ፤ የቁሳቁስ ስርጭቱ በተሳለጠ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በደገሀቡር ከተማ 38 የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸው በየምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርጫ ጣቢያዎችም የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን በመረከብ ላይ ይገኛሉ።
በምርጫው ድምጽ ለመስጠት 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወቃል፡፡
በቦርዱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።