በአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ክልሎች የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ ይገኛል።
የኢዜአ ሪፖርተሮች በከተማዋ በምርጫ ክልል 11 እና 12 እንዲሁም በሌሎች ምርጫ ጣቢያዎች የተለያዩ አካባቢዎች በአካል ተዘዋውረው እንደተመለከቱት፣ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ስር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ ስርጭቱ እየተከናወነ ነው።
በአብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች የግብዓት ሥርጭቱ እየተጠናቀቀ የሚገኝ ሲሆን፣ ለምርጫው ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ለመታዘብ ተችሏል።
ይህ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዜጎችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት በተግባር የሚያረጋግጥ ዋነኛ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው ነው።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
በጠቅላላ ምርጫው ድምጽ ለመስጠት በአጠቃላይ 54 ሚሊየን 57 ሺህ 861 መራጮች መመዝገባቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 438 ዕጩዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀው የክርክር መድረክ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳባቸውን ለህዝብ አድርሰዋል።
የምርጫውን ሂደት ለመታዘብም 55 ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ 26 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና 59 የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድና ዕውቅና አግኝተው የሥራ ስምሪት ወስደዋል።
በተጨማሪም ሰባተኛውን የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ የዘገባ ሽፋን ለመስጠት 56 የሀገር ውስጥ እና 12 የውጭ፣ በአጠቃላይ 68 መገናኛ ብዙኅን ፈቃድ መስጠቱን ቦርዱ አስታውቋል።
በተለያዩ የምርጫ ክልሎችም የምርጫ ማስፈፀሚያ የቁሳቁስ ሥርጭቱ በተያዘው መርሃ ግብር መሠረት ተደራሽ እየተደረገ በመሆኑ፣ ሀገሪቱ ለታሪካዊው ምርጫ ሙሉ ዝግጅቷን ማጠናቀቋ ሪፖርተሮቻችን በተዘዋወሩበት ምርጫ ክልሎች ተመልክተዋል።