ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል እያደረገ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ለጋራ ግብረ-ኃይሉ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት፣ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ለምርጫው ያደረገው ዝግጅት እጅግ ጠንካራ ነው።
ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ ቢሆንም፣ መከላከያ ሠራዊት ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ኃይሎች ጋር በመሆን እነዚህን የጥፋት ዕቅዶች ማክሸፉን አረጋግጠዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አክለውም፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሪፎርሙ በኋላ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ ትጥቅና በቴክኖሎጂ መደራጀቱ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና በተለይም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር መረጃዎችን በመለዋወጥና ከህዝቡ ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በቅድመ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችና የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ደህንነት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም፣ ቀሪውን የምርጫ ሂደት ሰላማዊነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ሎጂስቲክስ እና ትጥቆች መሟላታቸውን እንዲሁም ለተልዕኮው የሚመጥን በቂ ስልጠና እና ኦረንቴሽን የወሰደ የሰው ኃይል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መሰማራቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና ደህንነት የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከምርጫው በኋላ የሚከናወኑ ሂደቶችም በስኬት እንዲጠናቀቁ ግብረ-ኃይሉ ሙሉ ዝግጅት ማድረጉን ኮሚሽነር ጀነራሉ አረጋግጠዋል።