በሲዳማ ክልል የምርጫ ቁሶች እየተሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የምርጫ ቁሶች እየተሰራጩ ነው
ሀዋሳ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ወደምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጩ ይገኛል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች 54 ሚሊዮን 57 ሺህ 861 መራጮች የተመዘገቡበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መርሀግብር መሰረትም ለምርጫው አስፈላጊ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተው በአሁኑ ወቅት የምርጫ ቁሳቁስ በየምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ሥራ እየተከናወነ ነው።
በሲዳማ ክልል በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችም የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጩ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል።
በሲዳማ 19 የምርጫ ክልሎች እና 2ሺህ 266 የምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን በነዚህ የምርጫ ጣቢያዎችም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የማድረስ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በሃዋሳ ከተማ ባሉ ሁለት የምርጫ ክልሎች ስር 464 ምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ።
የኢዜአ ሪፖርተር በሀዋሳ ከተማ ዛሬ ባደረገው ምልከታም የምርጫ ቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎቹ እየተጓጓዙ መሆኑን ለማየት ችሏል።
በሲዳማ ክልል ጉጉማ ምርጫ ክልልም የምርጫ ቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የምርጫ ክልሉ አስፈጻሚ ደረጀ ደንግሶ ተናግረዋል።
በመጪው ሰኞ ለሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ ቅድመ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው የምርጫ ቁሶችም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በጉጉማ የምርጫ ክልል ሥር 78 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ የምርጫ ቁሳቁስ በተሽከርካሪዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ እየተጓጓዙ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለጠቅላላ ምርጫው ምቹና ዝግጁ እንዲሆኑ በጣቢያዎቹ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።