የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዜጎች በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነቡበትን ዕድል እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዜጎች በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነቡበትን ዕድል እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዜጎች በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነቡበትን ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በዜጎች መካከል ለዘመናት የዘለቁ መሰረታዊ የሃሳብ ልዩነቶችን በሰለጠነ ምክክር መፍትሔ በመስጠት ዘላቂ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ለዚህም በ2014 ዓ.ም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በአሁኑ ወቅት ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል አጀንዳ የማደራጀትና የግብዓት የማሰባሰብ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረስላሴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ የምክክር ሥርዓት መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ምኅዳር ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ያለፈባቸው ወሳኝ ምዕራፎችም በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ ምክክር በማድረግ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ዜጎችም በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ብሔራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት የሚችሉበትን ስልጡን የጠረጴዛ ዙሪያ ምክክር እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክር ሂደቱም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ የተለያዩ አመለካከቶችና አጀንዳዎች በነፃነት የሚንሸራሸርበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በማደራጀት ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ሀገራዊ ምክክር ጉዞ በዲጂታል አማራጭ ጭምር በመሰነድ ቀጣዩ ትውልድ ትምህርት እንዲቀስምበት ለማድረግ የመሰነድ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ሀገራዊ የምክክር ሂደት አሳታፊና አካታችነት በግልፅ እንደሚያሳይ ነው ጨምረው የተናገሩት።
የምክክር ሂደቱን የመሰነድ ሥራም ጥናትና ምርምርን ጨምሮ ለሌሎች ሀገራት ጭምር ልምድና ተሞክሮን ማጋራት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ሂደትም የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በማደራጀት ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ በይፋ ለማስጀመር የመጨረሻ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስገንዝበዋል።
በምክክር ሂደቱም የሁሉም የኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን ለውይይት በማቅረብ ብዝኅነትንና ሕብረ ብሔራዊነትን ታሳቢ አድርጎ የሚካሄድ መሆኑን አንስተዋል።
ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ አስፈላጊው የቴክኒክና የሎጀስቲክስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።