በወሰዱት ካርድ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የማልጋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በወሰዱት ካርድ ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የማልጋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
ውጅግራ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በወሰዱት ካርድ በምርጫው ዕለት ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን በሲዳማ ክልል የማልጋ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24/2018 ዓ/ም ይካሄዳል።
በምርጫው ለመሳተፍ ከ54 ሚሊዮን በላይ የሀገሪቱ ዜጎች ተመዝግበው ካርድ መውሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን 42 የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይወዳደራሉ።
በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን የማልጋ ወረዳ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፤ በዕለቱ ድምፅ በመስጠት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም ተዘጋጅተዋል።
ነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሰንበቴ ሽምቡሌ እንደገለጹት በምርጫው ለመሳተፍ የወሰዱትን ካርድ በጥንቃቄ በመያዝ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል፡፡
ምርጫው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚመራ መንግስት በድምጻችው የሚመርጡበት በመሆኑ ልዩ ትርጉም እንደሚሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡
ሌላኛው ነዋሪ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው በቀጣይ ሰኞ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከማለዳው 12:00 ጀምሮ በነቂስ ወጥተን ድምጻችንን ለመስጠት ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።
የአንድ ካርድ ድምጽ ከፍተኛ ዋጋ ያለው በመሆኑ በጥንቃቄ በመያዝ ተዘጋጅተን በመጠባበቅ ላይ ነን ነው ያሉት።
በወሰዱት ካርድ ሀገሪቱን ያሻግራል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተው የምርጫ ድምጽ መስጫ ቀኑን እየተጠባበቁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አቶ ብርሀኑ ቡታ ናቸው።
ሁሉም ዜጋ በወሰደው ካርድ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ድምጽ በመስጠት መጠቀም እንደሚገባውም መክረዋል፡፡
መምህር ሕዝቅኤል ብርሃኑ የተባሉ የወረዳው ነዋሪ በበኩላቸው ''የወሰድነው ካርድ ዋጋ የሚኖረው በዕለቱ ድምፅ ስንሰጥ ብቻ ነው'' ብለዋል፡፡
ዜጎች በዕለቱ በምርጫው ለፈለጉት ፓርቲ ድምጽ በመስጠት ካርዳቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡