በምርጫው ዕለት ድምፅ በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚናችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው ዕለት ድምፅ በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚናችንን እንወጣለን
አዳማ ፤ ግንቦት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በምርጫው ዕለት ድምፅ በመስጠት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚናችንን እንወጣለን ሲሉ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
ከአዳማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኢልሚያ ሱሌይማን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ጠቅላላ ምርጫው ዜጎች ለሀገራቸው የሚበጀውን መሪ በነፃነት በመምረጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚናቸውን የሚወጡበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያበቃቸውን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪ አቶ በቀለ በጅጋ በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት ካርድ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥር ፓርቲ ድምፁን ለመስጠት መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ በአዳማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወጣት ታምራት ለሜሳ ነው።
ህብረተሰቡ የወሰደውን ካርድ ሳያባክን በምርጫው ዕለት የሚበጀውን በመምረጥ በመብቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት ምክሩን ለግሷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።