ቀጥታ፡

በካርዳችን ይበጀናል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት የምርጫ ካርድ ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢዜአ ምርጫውን አስመልክቶ ካነጋገራቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አወቀ አስመቸ፤ ምርጫ በህዝብ ይሁንታ መንግሥት የሚመሰረትበት የፖለቲካ ሒደት ነው ብሏል፡፡

ስለ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ምንነት፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በቂ መረጃ እንዳገኘና ለሀገርና ለህዝብ የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ የሚያስችል ግንዛቤ መጨበጡን ገልጿል፡፡

በመሆኑም እንደ አንድ ዜጋ የድምጽ መስጫ ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ዮሐንስ መልኬ በበኩሉ፤ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ከምዝገባ እስከ ቅስቀሳ ድረስ ፍትሃዊና አሳታፊ እንደነበር መመልከቱን ገልጿል።

በመሆኑም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ወጣቶችን ያሳትፋል ብሎ የሚያምንበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የምርጫ ካርድ ምዝገባው አሳታፊና አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ እንደነበር የገለጸችው ደግሞ ወጣት ተስፋነሽ አክሊሉ ናት።

በመሰረተ ልማት፣ በትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ይሰራል ብዬ የማምንበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እለቱን እየተጠባበኩ እገኛለሁ ብላለች፡፡

ሌላኛው ወጣት ላቀው ስጦታው፤ አንድ ድምጽ ለሀገር ትልቅ ዋጋ እንዳለው በመረዳት ይበጃል ያለውን ፓርቲ ለመመረጥ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

ወጣት ፋሲካው እሸቱ በበኩሉ፤ የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለሚችል ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

ወይዘሮ ትዝታ ተስፋ እና ወይዘሮ እመቤት አለሙ ለመንግሥት ምስረታ በምርጫ መሳተፍ የዜግነት ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ ዕለቱን እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም